ማሳሰቢያ፡ ይህ ገጽ የተዘጋጀው የተለያዩ የኅብረተሰባችንን ሀሳብ ለመለዋወጫ እንጂ ለሚሰጡት ማንኛውም አስታየቶች በማንኛውም መንገድ ተጠያቂ አይደለም። ጉግል ድርጅትም ኃላፊነት አይወስድም። ኃላፊነቱ በሙሉ የአስታየት ሰጪው ብቻ ነው።
‹‹በጎውን ማን ያሳየናል የሚሉ ብዙ ናቸው››
(መዝ. 4፥6)፡፡
ስለ ዘመናችን ድንቅነት ብዙ ተነግሯል፡፡ የንግግሩ ምራቅ ሳይደርቅ ግን አሳዛኝነቱ ይተረካል፡፡ ዘመናችን ከተደነቀባቸው ነገሮች አንዱ የመረጃ ዘመን መሆኑ ነው፡፡ ሰዎች ስለ ራሳቸው ሳይሆን ስለ ሌሎች፣ ስለ ጎረቤታቸው ሳይሆን ስለ መካከለኛው ምሥራቅ ብዙ መረጃዎችን የሚሰሙበት ዘመን ነው፡፡ የመስማት አንዱ ዓላማ ለመመካከር፣ መራራው ወደ ጣፋጭ እንዲለወጥ ለመጸለይ ነው፡፡ የመረጃው ዘመን ግን ሰምቶ ማዳነቅ ብቻ ነው፡፡ ችግሮች ብዙ ናቸው፣ የመፍትሔ ድምፆች ግን አይሰሙም፡፡ ብዙ የመረጃ መረቦች የጭንቅ ወሬ ካጡ ይጨነቃሉ፡፡ የጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ የእርስ በርስ መተላለቅ ትልቅ ርእሳቸው ነው፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ በ1998 ዓ.ም በነበረው ግርግር አንድ የጋዜጣ አዘጋጅ ለጓደኛው ሲናገር፡- ‹‹ይህ ግርግር ሳይበርድ ለሦስት ወር ከቀጠለ የጀመርኩትን ቤት እጨርሳለሁ›› እንዳለ፣ ጭንቅ ባላለቀ እያሉ የሚሳሉ፣ እንደ ዕድር ጡሩንባ ነፊ ሞተ እንጂ ተነሣ የማይሉ፣ እንደ ጠመንጃ አፈ - ሙዝ ከአፋቸው ደህና የማይወጣ፣ ያልተባረኩ አንደበቶች በዝተዋል፡፡ ብዙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን እንለዋውጣለን፡፡ ሁሉም የሚያመነዥጉት ያንን ክፉ ነው፡፡ አዋቂዎቹ የሚሰጡት ትንታኔ የሚመጣውን ቀውስ ጠቋሚ ነው፡፡ ስለዚህ የግለሰቦች ቀውስ እያለፈ ዓለም ራሷ እየቀወሰች መሆኗን እንረዳለን፡፡ ግለሰቦች ሲቃወሱ ምድር ችላቸው ብዙ ዘመን ኖረናል፡፡ ምድር ከቀወሰች ግን ማን ይችላታል@
ተበልቶ እንዳለቀ አጥንት ወይም የበቆሎ ቆረቆንዳ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ብናገላብጣቸው ለጥጋብ የሚሆን አንድም ነገር የለባቸውም፡፡ ወደ ኢንተርኔት ጫካም ስንገባ ወሬ ከመንግሥታዊ ተቋማት ወደ ግለሰብ ተቋማት ዝቅ ብሎ፣ ‹‹ሐሜት ድሮ ቀረ በቃል ብቻ›› የሚሉ የጽሑፍ ሐሜተኞችን እናገኛለን፡፡ የሰውን ስም ቡና ላይ ከማንሣት ድረ - ገጽ ላይ ወደ ማንሣት ተሸጋግረናል፡፡ ብሔራዊ የነበረውን ኃጢአታችንን ዓለም አቀፋዊ አድርገነዋል፡፡ ጫካ ገብቶ በጥይት የመዋጋት ዘመን በኢንተርኔት ውስጥ መሽጎ በስም ማጥፋት አረር እንደ ተለወጠ እያየን ነው፡፡
ጉድ ያለበት የሰው ልጅ የሌላውን ጉድ ለማውራት በጀት የባጀተበት ዘመን መሆኑን እናያለን፡፡ ዘመኑና ሥልጣኔው መስተዋት ሳይሆን መነጽር መሆናቸውን እናስተውላለን፡፡ መስተዋት ራስን ያሳያል፣ መነጽር ሌላውን ያሳያል፡፡ በክፉ ወሬዎች በተከበበው ዘመን የብዙዎች ነፍስ ተጨንቃለች፡፡ በሩቅ ስላለው ሰው እያወቁ ራስን አለማወቅ፣ የሌሎችን ክፋት እየተረኩ የእግዚአብሔርን በጎነት መዘንጋት ለሰዎች ዕረፍትን አልሰጣቸውም፡፡ በእውነት፡- ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል@ የሚሉ ብዙዎች ናቸው›› (መዝ 4፥6)፡፡
ስለ ሰዎች ክፋት አንድ ሰዓት ማውራት መቻል ስለ እግዚአብሔር በጎነት ዐሥር ደቂቃ መነጋገር አለ መቻል በጣም ያሳዝናል፡፡ የሰው ልጅ የትኛውም ማንነቱ አያሳርፍም፡፡ እንኳን ከድካሙ ከብርታቱም ጉድለት አለበት፡፡ ነቢዩ፡- ‹‹ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው›› ያለው ለዚህ ነው (ኢሳ. 64.6)፡፡ የሚያሳርፈው የመስቀሉ ሥራ ብቻ ነው፡፡ ስለ ክፉ አንድ መጽሐፍ መጻፍ ስለ መጽናናት ግን አንድ መስመር አለመጻፍ በእውነት ምስኪንነት፣ የሞትም አገልጋይ መሆን ነው፡፡ የሰዎችን መልካምነት በካባ እየሸፈኑ ትንሽ ስህተታቸውን በአጉሊ መነጽር ማየት በእውነት አለመታደል ነው፡፡ ዘመናዊነትን ስናየው የክፋት ማፍጠኛ እንጂ የመልካም ነገር ማፍጠኛ አለመሆኑ ያሳዝናል፡፡
ብዙ የዓለማችን ሕዝቦች ከመረጃ መረቦች ራሳቸውን እያገለሉ ነው፡፡ የራሳቸውን ችግር ሳይፈቱ ስለ ሰው ኃጢአት መነጋገር እየሰለቹ ነው፡፡ ልክ ያልሆኑ ነገሮችን ከሚያሰሙ ስብከቶች ልክ የሆነውን ወደሚያሳዩ አገልጋዮች ዘወር እያሉ ነው፡፡ የሰው አእምሮ በብዙ ጭንቀቶች በተወጠረበት በዚህ ዘመን፣ ብዙ አደንዛዥ ዕፆች በሚወሰዱበት በዛሬው ጊዜ የሚበጀው ሰላማዊ መልእክት ብቻ ነው፡፡ በራሳቸው መወደድ ያልቻሉ ሌላውን እያስጠሉ ለመወደድ የሚሹ ሰዎችን ብዙዎች እየራቁ ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል@›› እያሉ ነው፡፡ እኔ ቆንጆ ነኝ ለማለት እገሌ አስቀያሚ ነው ማለት አስፈላጊ እንዳልሆነ ሕዝባችን እያስተዋለ ነው፡፡ እናንተን የምንቀበላችሁ በራሳችሁ ልክ ስትሆኑ እንጂ እነ እገሌ ስለ ተሳሳቱ አይደለም እያለ ነው፡፡ በእውነት ጠብን ሳይሆን ፍቅርን የሚዘሩ፣ ክርክርን ሳይሆን መግባባትን የሚያመጡ አገልጋዮች እየተፈለጉ ነው፡፡
ራሳችንን ስናየው ሬዲዮን በደንብ ሳንጠቀም ቴሌቪዥን የጀመርን፣ ታይፕን በደንብ ሳንጠቀም ኮምፒዩተርን የተከልን፣ አጠገባችን ካለው ሰው ጋር ሳንግባባ ዓለም አቀፍ መረጃ ውስጥ አሳብ የምንሰጥ፣ ከወንድማችን እየተጣላን ከዓለም አቀፍ ወጣቶች ጋር ማኅበርተኛ መሆን የምንፈልግ፣ በጾም ከበሮ መምታትን እየጠላን ወገናችንን በስድብ የምንደልቅ፣ ያጎረስነው ሰው እያነቀ በላይ በላዩ የምናጎርስ፣ ከሥልጣኔው ክፉውን የምንጠቀም ነን፡፡
በብዙ ውጣ ውረድ ያለፈው ሕዝባችን ዕረፍትን ፍለጋ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ በሁከት ድምፅ እያሸበርነው፣ ማንንም አትመን እያልን አውሬን እየሳልንለት፣ የሥጋ ቅንዓታችንን ሃይማኖታዊ ካባ አልብሰን እያስጨነቅነው ነው፡፡ ወጣትነቱን በትክክለኛ ጎዳና ለመምራት የመጣውን ወጣት ሃይማኖታዊ ጠብ እንዲጣላ፣ በዝማሬ በስብከት ካጽናኑት አገልጋዮች ጋር እንዲታኮስ እያደረግነው ነው፡፡ ከዓለም ሁከትን ሸሽቶ የመጣው ትውልድ፣ በቤተ ክርስቲያን የሁከትን ድምፅ ሲሰማ ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል@›› እያለ እየተጨነቀ ነው፡፡ ያሉት አገልጋዮች ተቀንሰው አይደለም፣ በእጥፍ ተጨምረው እንኳ ሕዝቡን መድረስ አይቻልም፡፡ ከዚሁም ላይ ስም እየሰጠን እየቀነስን ቤተ ክርስቲያንን የወላድ መሐን ማድረጋችን፣ የመናፍቃኑን አዳራሽ አለመሙላት ከውስጥ መግፋታችን አሳዛኝ ነው፡፡ ብዙ የሳጥናኤል የውስጥ ካድሬዎች ከውስጥ ሆነው ሲገፉ ከደጅ ያሉት ደግሞ ይቀበላሉ፡፡ በዋጋ የተሰበሰበውን ሕዝብ ያለ ዋጋ መበተን፣ ፍቅር አጥቶ ከዓለም የመጣውን ሕዝብ ጠብና ክርክር ማስጠናት ተገቢ አይደለም፡፡ አንድ ሕገ መንግሥት (መጽሐፍ ቅዱስ) ይዘን መለያየት ለአረማውያን ሰይፍ ራሳችንን ማዘጋጀት ነው፡፡
ሕዝባችን የፍቅር ሰባኪዎች ሲፋቀሩ፣ የይቅርታ አዋጅ ነጋሪዎች ይቅር ሲባባሉ ማየት ይፈልጋል፡፡ የቃል ስብከታችንን ከተማው ጠግቦት በሕይወታችን ስንኖረው ማየት እየፈለገ ነው፡፡ በየአድባራቱ እየታየ ያለው የጠብ አዝመራ፣ ጭር ሲል የማይወዱት የጠብ ጫሪዎች፣ በሰው ሬሳ ለመኖር የሚያቅዱ የክርስቶስ ጠላቶች፣ ስሜታቸውን መግዛት ያቃታቸው የገምቦኞች ክተት ነው፡፡ ሕዝባችን የእግዚአብሔርን ቃል ዳኛ አድርጎ ማነው የሳተው? ማለት አለበት፡፡ ጋዜጣ ላይ የወጣ ሁሉ የመጨረሻው እውነት ሆኖ ሊታየው፣ በኢንተርኔት የተለቀቀ ሐሜት የሲኖዶስ ውሳኔ አድርጎ ሊቀበለው አይገባም፡፡ ሁሉን የሚበክሉ ሚዛን የለሾች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ከመልካም አገልጋዮች ብቻ ሳይሆን ከተሰቀለው ጌታ ሊለዩአት የተነሡ፣ ወንጌልን ከኦሪት፣ ክርስቶስን ከሙሴ፣ መጽሐፍን ከተረት መለየት ያልቻሉ፣ እውነት በሚመሰል ሐሰት፣ ቅንዓተ ቤተ ክርስቲያን በሚመስል ራስን መስበክ ሕዝቡን እያደናገሩት ይገኛሉ፡፡ ሕዝቡም የሚይዘውን የሚጨብጠውን አጥቶ ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል@›› ይላል፡፡
ወገናችን ዕድሜውን በሙሉ ብዙ ጭንቆችን ያየ፣ ብዙ ጦርነቶችን ያሳለፈ፣ የኑሮ ጠባሳ መልኩን ያጠፋው፣ በብዙ ቀBስለትም የሚያቃስት ነው፡፡ በዚህች አገር ላይ የኖረ፣ ያለፉትን ዘመናት ሰቆቃ ያየ ወገን፣ ሕዝቡን እንደ ገና አያስጨንቅም፡፡ የሚያጽናናውን ወንጌል በመስበክ ያረጋጋ ነበር፡፡ ጭጋግና ደመናው ነገን አላሳይ ላለው ወገን፣ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ላደከሙት ሕዝብ የወንጌልን ማዕድ የምናቀርብበት ዘመን አሁን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን መወከል የማይችሉ አጽራረ ወንጌሎች የአዋቂዎችን ልብ እየሰበሩት፣ ትውልዱ ያዳነውን ጌታ እንዳያይ የክርስቶስን ደም እያክፋፉበት መሆኑ ያሳዝናል፡፡ መሳሳት የማይደክማቸው፣ ከትላንት ጥፋት የማይማሩ በመሆናቸው ሊለቀስላቸው ይገባል፡፡ ሊሰበክ ሊታወቅ የሚገባው ማን ነው@ የቤተ ክርስቲያን መሠረትና ጉልላትስ ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለምን? ‹‹ሞኝ ባያፍር ዘመዱ ያፍራል›› እንዲሉ በእነዚህ ሰዎች እስከ መቼ እናፍራለን? በአይሁድ ምኩራብ ክርስቶስ በተስፋ ይሰበካል፣ አይታፈርበትም፡፡ በእስላም መስጊድ ዒሳ ተብሎ ይነሣል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ዘንድ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን የጠራ በውግረት ይሙት ተብሎ ይፈረድበታል፡፡ ጠላትነታቸው ከፍጡር ሳይሆን ከተሰቀለው ጌታ ጋር ነውና ንስሐ እንዲገቡ እንጋብዛለን፡፡ ነፍሳቸውም በሐዋርያት ውግዘት ውስጥ ነች፡- ‹‹ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን›› (1ቆሮ. 16.22) በተባለው ቃል የታሠሩ ናቸው፡፡
ሕዝቡ በዕንባ የሚዘምረውን ዝማሬ ያንተ አይደለም ይሉታል፣ የራሱ ያልሆነ ነገር እንዴት ያስለቅሰዋል? ልቡን ያሳረፉለትን ሰባኪዎች መናፍቃን ናቸው ይሉታል፣ የተፈወሰበትን መጻሕፍት የባዕድ ናቸው ይሉታል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ‹በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው›› (መዝ 4፥6)፡፡
ሕዝባችንም አደባባዩን የያዙ እውነተኞች ናቸው ብሎ ማሰብ የለበትም፡፡ ቅንዓት በዲግሪም አይለቅምና አዋቂዎች ነን በሚሉ ፈሪሳውያን ግራ ሊጋባ አይገባውም፡፡ እውነት ምንድነው? ብሎ ሊጠይቅ፣ ክርስቶስን የማይወድ የተረገመ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ ትላንት ያስተማሩት አገልጋዮች ዛሬ ጦርነት ሲታወጅባቸው የአንዱን ቀን ማጽናናታቸውን እንኳ አስቦ ለምን@ ሊል ይገባዋል፡፡ ባለቤቱ፡- ‹‹እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ›› እያለ አይደለህም ማን ይለዋል? እነዚህስ ስም አጥፊዎች ይህንን እንዲያደርጉ ፈቃድ የሰጣቸውና የወከላቸው አካል ማን ነው@ ማለት አለበት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በመግለጥ ሁሉንም አገልጋዮች በቃሉ መመዘን ይገባል፡፡ አሊያ ያለፉት ዘመናት ስህተት ሳያንስ ሌላ ደም በእጃችን እንዳይገኝ መጠንቀቅ ይገባል፡፡
ከዚህ በላይ የቀረበው ጥሁፍ ከhttp://dejesemay.org/ ገፅ የተወሰደ መሆኑን እናረጋግጣለን።
ይህን ጥሁፍ የለጠፍንበትም ምክንያት የምንሰራውን ሁሉ በመመርመር እንድናስተውል ይረዳን ዘንድ ሲሆን ከኛ የተለየ ሀሳብ ላላቸውና ለተለየ አላማ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ እየፈጸሙ ላለው እጸጽ ፣ ፈጣሪ አስታግሶ የመመርመርና የማስተዋሉን ልቦና እንዲሰጥልን ነው።
እኛ ገፃችንን ከከፈትንበት ዕለት ጀምሮ፤ ገጻችን የኮነነቻቸው ወንድሞችና እህቶችን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም አንጀት አስለቅሳለች። ለጀብዱ ሳይሆን ገጿ ከልቧ በቅንንነት ላደረገችው ማንኛውም እጸጽ ዛሬም ይቅርታን ትጠይቃለች። በአንጻሩም ያበረከተችውና እያበረከተች ያለችሁን በጎ ጎኗን ሳይዘነጋላት እንዴት አስተዋጾ ማድረግ እንደምትችል ከላይ የለጠፈችውንም ቅጂ በማስተዋል የተሻለ ግልጋሎትን ይስጣት እንላለን።
የተወደዳችሁ የገጻችን ተከታታዮች እንደምን ከርማችኃል? በእርሱ ፈቃድ ዛሬም ወዶ ለፈቀድልንና ዳግም በዚች ጦመር ላገናኘን ለልዑል እግዜአብሄር ክብርና ምስጋና ይሁን። አሜን። የዳላሱ ቅዱስ ሚካኤል ሠይፍ ተባባሪያችንም እንዴት የደመቀ ጉባኤና የሰኔ ሚካኤል በዐለ ንግሥ እንዳሳለፋችሁ ያካፈለን ውብ ነውና ለዚህም ፈቃዱን ላደረገላችሁ ለልዑል እግዜአብሔር ክብር ምስጋን እስከ ዘለዓለም ይሁን።አሜን።
ለዚሁ በዐል ተጋብዛ ከቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የመጣችውን ዘማሪ ቪዛ እንዳይሰጣት የነበረውን የጠላት ሥራ ከሽፎ ለመጀመሪያ ጊዜ በምድረ አሜሪካ በዳላስ የቅዱስ ሚካኤል ደብር መገኘት ያመማቸው፤ ዘማሪ ዘርፌን ለማብጠልጠል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። እርሷ ግን ወደ አለም ገብቼ እግዜአብሄር የሰጠኝን ጸጋ ዋጋ አላሳጣውም በማለት በመንፈሳዊው ዝማሬዋና ግልጋሎቷ እየተባረካችሁበት መሆኑን ነው። ሌላው ኢላማቸው ደግሞ ከአትላንታ የመጣውን መምህር ልዑለቃል ላይ ነበር። ዛሬም በሕይወት ያሉና እስከ ጳጳስነት የበቁ ታላላቅ አባቶች ስር ከቆሎ ተማሪ ጀምሮ በሥርዐት አርቀው አሉን ከምንላቸው የቤተክርስትያናችን ሊቅ ተራ ያደረሱት መምህር ነው። አሜሪካ ከመጣም በኃላ ተመልሶ በቅድስት ሀገር ለአመታት ቤተክርስትያናችንን አገልግሎት ሰጥቶ የተመለሰና አሁንም በአትላንታ ክሚሰጠው መንፈሳዊ ግልጋሎት ጎን ለጎን እራሱን ወደ ከፍተኛ ተቋም ትምህርት በማሳተፍ ላይ የሚገኝና የቤተክርስትያናችን ተስፋ የጣለችበት ሊቃችን ነው በሚል በቂ የሆነ ማብራሪያን ያካፈለን የሚካኤል ሠይፍ አባል ነው። እንግዲህ እነዚህን ብርቅዬዎቻችን ላይ የተነጣጠረው ደባ ቤተክርስትያናችንን የወላድ መካን ለማድረግና ብቃት ያላቸውን አገልጋዮቻችንን በማራቅ የኦርቶዶክሳዊ እምነትን አዳክሞ ለማጥፋት የተከፈተና እየተካሄደ ያለ ሰይጣናዊ ምግባር ነው።
እነዚሁ በኦርቶዶክስ ካባ ስር በቤተክርስትያናችን ውስጥ የተሰገሰጉትን ለይቶ በማወቅ ማስወገድ ተገቢ ነው። በተለይም በምህጻር ቃል ’ማቅ’ ወይንም ማህበረ ቅዱሳን የተባለው ቡድን በቁጥር 1 የሚጠቀስና ንጹሀንን በማሳሳት ወደ እርሱ ጎራ በማስገባት መሳሪያ ማድረግ፣ ደካማና ለመተዳደሪያ በአገልግሎት ላይ የተሰማሩትንና በፈተና የወደቁትን በመለየት ድክመታቸውን ጨብጦ ማሰፈራሪያ በማድረግ የእርሱ የግዳጅ ሰለባ ያደረጋቸው ሲሆኑ፤ አንተባበር ያሉትን ደግሞ የተለያየ ስም በመስጠት ከቤተ ክርስትያኗ እንዲገለሉ ማድረግ፣ ያልተወገዘውን ተወግዟል፣ ያልተኮነነውን ተኮንኗል፣ ያልሰረቀውን ሌባ፣ የመሳሰለውን ሀሰታዊ ዘመቻቸውን በቃልና በጥሁፍ በተለያየ መንገድ በማሰራጨት ይፈጽማል። ለምሳሌ በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ደብር ውስጥ ተሰግስገው የነበሩትና ቤተክርስትያኑን በንዋይ ሲያደሙ፣ የደብሩ ተቀጣሪና ፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን በመያዝ፣ ድርጅታቸው በሰሜን አሜሪካ እንዲያብብ ዋሻ በማድረግ፣ እንዳይታወቅባቸው ጥያቄ ባነሳ ምዕመን ላይ የሀሰት ስም በመስጠት መከፋፈል፣ በካህናቱና በምዕመኑ መካከል ልዩነትን መፍጠር፣ የትምህርት ኮሚቴውን በመቆጣጠር የሚጋበዘው መምህር የእነርሱ አባል ብቻ መሆን እንዳለበት፣ ሌላው በእነርሱ መናፍቅ ስም እየተሰጠው ሲገለል፣ ወዘተ…. ያደረሱት በደል ገሀድ እየወጣ ሲመጣና ድርጊታቸው ተወግዞ ድርጅታቸው ሲገለል ፣ ወተት ያቆመች ጥገት ላም አድርገው ደብሩ እኛን ካስከፋ በፈለገውም መንገድ ቢሆን መንጠቅ ካልሆነም ማዘጋትና ማጥፋት በሚል መርሆ የጀመረውን የነውጥና የሀሴት መንገድን ነበር በሜይ 2ቀን 2010 በደብራችሁ የተመራውን ሁከት የፈጠረው።
ይህ ቡድን በግምባር ቀደምነት ያስተባበረውና የመራው ሁከት፤ በእግዜብሄር ቸርነትና ጥበቃ የረባም ንብረት ውድመት ወይንም ምንም አይነት የሕይወትም ሆነ አካል ጉዳት ሳይፈጠር ቀርቶ ሰይጣናዊ እቅዳቸው ለመክሸፍ ቢበቃም ጠባሳው ዛሬም የኦርቶዶክስን ልጆች ያቃጥላል። ሁከት እቅድ አውጪ፣ አስተባባሪና መሪ ፣ ተዋናያን፣ በፊልም ቀራጭና አራብቶ በዓለም ዙርይ በኢንተርኔት መልቀቅና ሕዝበ ክርስትያኑን ማሳዘንና አንገት ማስደፋት እውነትም እንደ ስሙ ‘ማህበረ ቅዱስ’ ወይስ ኅማህበረ ሰይጣን’ ? የሚለውን ለአንባቢያን ግንዛቤ እንተወዋለን።
ከዚህ ወጣ ብለን ደግሞ መነጋገሪ የሆነው የ240 ሺህ ዶላር ለጋሹ ይመለስልኝ ብለዋል ተብሎ በሰሜን አሜሪካን ወገኖቻችን መካከል መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ ነው። ስጦታው መደረጉን በእርግጥ ተረጋግጧል። እንግዲህ ለጋሹ የንግድ ድርጅት ሆኖ ተለጋሹ የግብረ-ሰናይ ድርጅት ለተቀበለው የንዋይ ድጎማ ምንም አይነት ቅድመ ውል የሚያስገድደው እስከሌለ ድረስ ባሻው መንገድ የድርጅቱን መርሆ በተከተለ ጥቅም ላይ የማዋል ሙሉ መብት አለው። ስለዚህም ቀደም ብለው የሰሜን አሜሪካን የኢትዮጵያን አመታዊ የእስፖርትና የባሕል ዝግጅት አመራር ውስጥ ከነበሩና የግል ጥቅም የቀረባቸው የፈጠሩት እንጂ ምንም አይነት የሕግ ጭብጥ የማይገባው አሉባልታ ብቻ ይሆናል የሚል ግምትን አሳስቦናል። በንግድም ሆነ በግብረ-ሰናይ ድርጅት የሚተዳደሩ ሁሉ ግብር ሰብሳቢው አካል ያስቀመጠውን ሕግ በመከተል ሁለቱም ወገን በተፈቀደላቸው የጊዜ ገደብ በመጠቀም ወጪና ገቢያቸውን አስታውቀውል የሚል እምነት ስላለን፤ ግርግር ፈጥሮ ለመቀራመት ያሰቡ ይታቀቡ እንላለን።
ይህ አይነቱ አሉታን የሚያመጡ ሥነ-ምግባሮች ለተቋሞች እክል በመሆን የውስጥን አለመግባባት አልፎ ሕልውናቸውንም እስከማጣት አድርሷቸዋል። አንዳንዶችም በማዕበሉ ተውጠው ለመትረፍ ትግል ላይ ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥም የዳላሱ የኢትዮጵያ መረዳጃ ማህበር ሲሆን ወይ በቅርቡ ሰምጦ ይጠፋል አሊያም በእድሩ ይተካል፣ ይህንን ቢያልፍ ደግሞ አብቦ ጤናማ ድርጅት ይወጣዋል። ከማዕበሉ ለጊዜው ተርፎ የየብሱን ጠርዝ የጨበጠውና ከማዕበሉ እየራቀ ያለው ደግሞ የዳላስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ደብር ነው። ይህ ክስተት በዙ ተመሳሳይ የኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ተቋማት በሰሜን አሜሪካ ይስተዋላል። ቅንነት ጠፍቶ በተንኮል፣ ምቀኝነትና ግለኝነት ከተተካ ውጤቱ መልካም አይሆንም።
ለማጠቃለያ ከጁን 7 እስክ 9/2011 በዳላስ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ደብረ ምህረት ካቴድራል ደብር ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በታሪክነቱ ታላቅ ሥፍራን የሚይዝና ለኢትዮጵያን ፣ ለትውልደ ኢትዮጵያን ለሆኑትና ላልሆኑት ያካተተና የኦርቶዶክሳዊ እምነት ተከታዮች በሆኑ ወጣቶችን በአንድነት የሚካሄድ ሀይማኖታዊ ጉባኤ ይደረጋል። ቀዳሚት ጁን 9/2011 ጠዋት በደብሩ የሚካሄደው ቅዳሴ ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እንደሚሆንና ትምህርቱም በተመሳሳይ መንግድ እንደሚስተናገድ አብሮን የደረሰን ዘገባ ይገልጣል። ከተሳታፊዎቹ መካከል የግብፅ፣ የግሪክ፣ የኦሬንታል፣ የህንድ፣ ወዘተ….እንደሚያካትት ተረድተናልና። ላዘጋጁ ደብርና ምዕመን እንኳን ለዚህ አደረሳችሁ ስንል ፤ ለተሳታፊዎችም የመልካም መተዋወቂያና ለወደፊቱ ለሚኖራቸው ሕብረት መሠረት መጣያ ወቅት እንዲሆን ምኞታችንና ፀሎታችን ነው። የአንድ እምነት ተከታዮች ሆነን ነገር ግን በአባቶች መለያየት ምክንያት እራሳችንን ከክርስቶስ እምነት መለየት እንደማይቻልና እርሱን ብቻ አምነን ከዚህና ከተመሳሳይ ጉባኤ እራስን ማገለልን ብሎም ከበረከቱ አለመሳተፍና አልፎም ማብጠልጠል ፍጹም ይለያልና ከክርስቶስ ይልቅ ለአባቶች ያደሩት እራሳቸውን ይመርምሩ እንላለን።
ያስተማረን የመከረን በዚህች ገጽ ላይ ከብዕራችን ጫፍ የጨመቅነውንና ከሌላም የቀላወጥነውን አዋህዶ ለናንተ ለመቸር የፈቀደውን እግዜአብሔር ለገናናው ስሙ አሁንም ክብር ምስጋና ይሁን። አሜን።
እርሶስ ምን ይላሉ?