ማሳሰቢያ፡ ይህ ገጽ የተዘጋጀው የተለያዩ የኅብረተሰባችንን ሀሳብ ለመለዋወጫ እንጂ ለሚሰጡት ማንኛውም አስታየቶች በማንኛውም መንገድ ተጠያቂ አይደለም። ጉግል ድርጅትም ኃላፊነት አይወስድም። ኃላፊነቱ በሙሉ የአስታየት ሰጪው ብቻ ነው።
በእውነት ለትውልድ ሀገራችንና ወገናችን እንስባለን?
ዝምታ ወርቅ ነው ሲባል ነበር ያደግነው። ዛሬ ደግሞ ዝምታ ጎጂ ወይም ካለመናገር ደጅ አዝማችነት ይቀራል የሚለውንም አባባል ጨምሮ በየፈርጁ ከተጠቀምንበት መልካም ውጤት ለማየት ያበቃናል። እንደምን አላችሁልን? እናንተንም እንደኛ አቅፎና ደግፎ በፀጋና በምሕረቱ ተንከባክቦ ዳግመኛ በዚህ ገጽ ለመገናኘት ፈቃዱ ለሆነና ቀጣዩንም ዕድሜ ደግሞ ፈቃዱ ከኛ እንዲሆን፣ ይህንንም ዓብይ ጾም በሰላም አስጀምሮ በሰላም እንዲያስጨርሰን፤ የምናቀርብለትን ጾምና ጸሎት እንዲቀበለን፤ ይቅርታን ምሕረቱን እንዲያበዛልን፤ ልባችንና አንደበታችንን እንዲገዛልን፤ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ፣ በድፍረትሆነ በስህተት ያሳዘነውም ሆነ የበደልነው ቢኖር ይቅር ይለን ዘንድ፤ እኛም የተቆጣንበት ወንድም ይሁን ሴት ከልባችን ይቅር እንል ዘንድ ልቦናችን ያስገዛልን፤ ሁላችንንም በስላምና በፍቅር አንድ አድርጎ ይጠብቅልን፤ አጽራረ ቤተክርስትያንን አስታግስልን፣ እያልን በታላቁና ገናና ስምህ እንማጸንህ ዘንድ ፈቃድህ ስለሆነ ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁንልን። አሜን።
አንድ ታዳሚያችን ከሰደደልን ጥሁፍ በመነሳት ባለፈው ዕለተ ሰንበት ከቅዳሴ በኃላ በስለት ስም ይነገርልኝ ብለው ለመጋቢው ካሕን ያቀረቡትን ጥሁፍና የካሕኑን መልስ የሰማው ምዕመንም በግለሰቡ ገፋፊነት የተሞከረው ኾነ ተብሎ offensive language ያለቦታው ለመጠቀም በመሆኑና እራሱን የቻለ አጀንዳ ያለው በመሆኑ ከላይ እንዳስቀመጥነው፤ ዝምታ ወርቅ ነው የሚለውን እናሰምርበታለን። ይሁንና በዚህ የዐብይ ጾም ለሁላችንም ማስተዋልን ሰጥቶ፤ ጌታ በምሳሌ 50 መንጋዎች ውስጥ አንድ ቢጠፋበት ለፍለጋ 49ኙን ትቶ በመሄድ እንዳስተማርን ፤ እኛም ከልባችን የጠፋውን ፍልጋ በጾምና በጸሎት መትጋትና ስናገኝም እጆቻችንን ዘርግተን መቀበል እንዳለብን ገጻችን በጥያቄ ለሁላችንም ያስተላልፋል?
ከዚሁ በተጓዳኝ እራስን ወይንም ቅሬታን በመግለጽ የሚያመጣውን ውጤት በአለማችን ዙሪያ እየተካሄደ ያለውን ነውጥ ስንዳስስ ከግለሰብ አልፎ ሀገርና አህጉርን እያተራመሰ ነው። ችግሮችና ብሶቶች በዘመናዊውና ቴክኖሎጂ ወለድ በሆነው መንገድ ሁሉ መጠቀም የግድ ሆኖ ለአመታት ሙጥኝ ብለው የራሳቸውን ሀገርና ሕዝብ ሲበድሉ የኖሩ በሕዝብ ተቃውሞ የሥልጣናቸው ሁሉ ፍጻሜ ሲሆን፣ ጎራቸው እየታመሰ ያሉትም አምባገነኖች እንደዚሁ ቀናቸውን እየቆጠሩ ይገኛሉ። ከአረቡ ሀገራት ብዙም የማትርቀው የኛው ኢትዮጵያ መብት መርገጥ የጀመረችው ከንጉሣዊው ዘመነ መንግሥት ቢሆንም ባለፈው 40 አመታት ውስጥ ከዘመን ወደ ዘመን እየባሰበትና እየከፋ የመጣው የሕዝቦች ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በኃይል መስበርን ሲተገበር በማየት እንዲሁም የዚሁ ሰለባ በመሆን ለስደት የተዳረግን ሁሉ የገፈቱ ቀማሾችና እማኞች ለመሆን አብቅቶናል።
ዛሬ እኛና እናንተ በዚህ ገጽ አማካኝነት እንደልባችን ሀሳባችንን ብቻ ሳይሆን ያለውንም ዕውነታ ለመለዋወጫ መጠቀሚያ መስመር በመሆን ስንጠቀም፤ ከዚሁ ጋር ዘመን ያመጣውን ጥበብ በመጠቀም ብሎግ፣ ፌስቡክ፣ ቲውተርና ዩ ቲዩብ ጥቂቶች ናቸው።
አምባገነን መሪዎች ግን በእጃቸው ያለውን ይህን ጥበብ ከሕዝባቸው አንቀው የሥልጣን እድሜ ያራዘሙ የመሰላቸው ሁሉ ቀኑ እየመሸባቸው ይገኛል። ባለፈው አመት ለአለም ትዝብት የበቃውና አስቂኝ የሆነው የትውልድ ሀገራችንን ብሔራዊ ምርጫ ውጤትዛሬም እውነተኛና ሕዝባዊ ነው የሚሉ አይነ ደረቆች ካሉ እንደ አምባገነኖች አእምሮ ራሳቸውን wire ያደርጉ ወይንም የስነ ልቦና ችግር ያለባቸው ብቻ ናቸው። እነዚህም ለነዚህ ጓጉንቸር መሪዎች የቀረቡና የሥልጣን ሸሪኮች፣ የጥቅም ተካፍዮችና ቅጥረኞች ሲሆኑ ምንም አይነት የሞራል ግዴታን የማያውቁ ራሳቸውን ያሳወሩ ብቻ ናቸው።
አንዳንድ ፖለቲከኞች በሰሜን አፍሪካ ተጀምሮ በአረቡ አህጉር የተቀጣጠለው አብዮት ለኢትዮጵያም እንዲደርስ ቅስቀሳ ጀምረዋል። ነገር ግን አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የለገሰ ዜናዊ አስተዳደር እዚህ ይደርሳል ተብሎ ያሰበ ማንም አልነበርም እቅድም የለም። በዚህ ወር 36 አመት ይሞላዋል የሚባለው ድርጅት በልደት በአል ስም ኬክ ሊቃመሱ ቀርቶ ፕላን ቁጥር 1, 2, 3, ወዘተ እያለ የሕዝብ አመጽን መግታት ካልቻለ የትኛው ሀገር ይቀበለኝ ይሆን? በማለት በሽብር ላይ መሆኑን የሚደርሱን ዘገባዎች ይጠቁሟሉ። ከጅምሩ እነ አባይ ጸሀይ የትግራይ ነጻ አውጪ ብለው ለጠባብና ለአንድ ጠቅላይ ግዛት የመገንጠል ነጻነት ብቻ ነበር። ያንን ካሟሉ በኃላ ፤ ከሌሎች ገንጣይ ቡድኖች ጋር ሆነው ሀገር ለመገነጣጠል ባደርጉት እንቅስቃሴ ትግል መዲናዋን ለመጨበጥና ራሳቸውንም ለማስቀመጥ ያበቁት። በለስ ቀንቷቸው በትረ መንግሥቱን ቢጨብጡም የነበረውን የወታደራዊ መዋቀር መበተንና የገቡትን የመጀመሪያውን ሀገርን የመገንጠል ኮንትራት እውነታ የፈጸሙት። ይህ በዚህ እንዳለ ወታደራዊ አመራሩም በአንድ ብሔር ቁጥጥር ሥር ወድቆ ፣ ጠበንጃ ያነሳውም ተቃዋሚ በዘርና በጎሳ ጠባብ አመለካከትና ከሌላው ብሔር ጋር ለመተባበር እምነት አልባ የሆነ፣ የተላያዩ በሀገር ውስጥ አለን የሚሉ ተቃዋሚ ሀይሎች እንደ ውጪዎቹ በወረቀት ላይ ብቻ የሰፈሩ ስሞች በሆኑበት ሰአት፤ ሕዝቡ ያንገሸገሸውን የትግሬ ነጻ አውጪ ተሳክቶለት በአመጽ ቢጥል የተዘጋጀ ተረካቢ ማነው? ሰላምና ፀጥታ መሰረታዊና ቅድሚያ የሚሰጠው ሲሆን፣ ተቃዋሚ ነን ወይንም ለውጥ እንፈልጋለን የሚሉ ወገኖች ሁሉ ምን ያህል ground work አጠናቀዋል? ምንስ ያህሉ የጸጥታ አስከባሪው ክፍል ተባባሪ ሊሆን ይችላል? ጊዜያዊ አመራሩንስ እነማን ይይዛሉ? በእርግጥስ ለሕዝቡ ያስረክባሉን? የመሳሰሉትን ጥያቄዎችን ከወዲሁ ማላመጥ ተገቢ ይመስለናል።
በሌላው በኩል የነዚሁ አንባገነን መሪዎች ተቀጣሪና አራማጅ የሆኑትን በቅርቡ በአለም ዙሪያ ለሰበካ የሚያሰራጨው የትግሬ ነጻ አውጪ እንደተጠበቀ ሆኖ አብረውን ከኛ ጋራ የሚኖሩ ሌሎቹ ቅጥረኞች በተሰጣቸው የሥራ ድልድል፤ የኛ የሆኑት ድርጅቶች ውስጥ ጠልቀው በመግባት ቁልፍ የሆኑትን ቦታዎችን መያዝ ነው። በራሱምግባር የማይተማመን መንግሥት በውጪ የሚገኙትን ተወላጆች በሙሉ ተቃዋሚ መስለው ስለሚታዩት፣ በፍራቻ ብቻ በተለያየ ጥቅማ ጥቅም በመደለል በነጻ የተሰጣቸው ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ለጥቅም ታውረው በአንድ ወቅት እሽቅድድም ከገቡት ውስጥ ከስረው የተመለሱት አያሌ ሲሆኑ፤ ለንዋይ ብለውም ህሊናቸውን ሸጠው በባንዳነት ያደሩም አሉ። ይህ ከፋፍለህ ግዛ መርህ በትውልድ ሀገራቸው ከእለት ወደ እለት ገፈት ቀማሽ የሆኑት ዜጎች ግን በገንዘባቸው እንኳ የተነፈጉት፣ ቅድሚያ ውጪ ለሚኖሩት ወይንም ለሥርዐቱ አንቋላጮች ብቻ በመደረጉ፣ ከመንግሥት ትብብር ለማግኘት እኛም ሀገር ለቀን መሰደድ አለብን ? እያሉ መጠየቅ ከተጀመረ አመታትን እያስቆጠረ ነው።
በዳላስ ከተማም ቢሆን ቅጥረኞች መጀመርያ ያደረጉት የዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ደብርን በመቆጣጠር በአማኒዎች መካከል ለትግሬ ነጻ አውጪ የስለላ ስራዎችን ማካሄድንና ተቃዋሚዎችን ማብከን፣ የሀሰት አሉባልታን መክፈት፣ ከህብረተሰቡ የሚገለሉበትን ማንኛውንም አይነት ዘመቻ ማካሄድና በሀገር ቤት ባሉ ዘመዶቻቸው ላይ ሽብርን መፍጠር ነው። ይኼንን ለማድረግ የጀመሩት ሳይሳካ ሲቀር፣ አጽራረ ቤተ ክርስትያን ከሆኑት ጎራ በመቀላቀልና በአንድ በኩል ደብሩንና አስተዳዳሪዎችን በመክሰስና በማስከሰስ ፣ በሌላ በኩል የሰላም ኮሜቴ በማለት በቅዠት ጎዳና ብቻቸውን በመቅረታቸው፤ ዛሬ በዳላስና ፎርትዎርዝ የኢትዮጵያን መረዳጃ ማህበርን ለመያዝ የመጨረሻ ትግላቸውን ከፍተዋል።
ባለፈው እንዳስነበብነው ሁሉ ለ30 አመት የመረዳጃ ማህበሩ በየጊዜው የሚለዋውጡት አመራሮች ለተለያየ የፖለቲካ ተግባር እንጂ ለህብረተሰቡ ይህን አደረኩኝ ብሎ የሰራው ጉልህ አስተዋጾ ለመጥቀስ የሚያዳዳን አንዳችም የለም። በተለይ በቅርቡ ወደ ከተማው የዘለቁና ይህንኑ ድርጅት ሽፋን በማድረግ የራሳቸውን ግብረሰናይ ድርጅት በመክፈት የመረዳጃ ማህበሩ የገቢ ምንጭና የህብረተሰቡን ስም ለራሳቸው መጠቀሚያ እያደርጉ መሆናቸውን ባለፈው ጥሁፋችን ያሰመርንበት ነጥብ ነው። በቅርቡም በማርች 5 ያዘጋጀው ዝግጅት ወጪው በሙሉ በስፖንሰሩ የተሸፈነ ሲሆን ሕብረተሰባችንን ይጠቅማል ከተባለ የቅዱስ ሚካኤል አዳራሽ ወይንም የሌላው በነጻ መጠቀም ሲቻልና መረዳጃው ማህበሩም ቢሆን በተጠቀመ ነበር። ቀጥረናታል የተባለችውም የቢሮዋ ሰራተኛም ቢሆን ይህን የመሳሰለ ለሕብረተሰቡ ይጠቅማሉ የተባሉትን ዝግጅቶች ማመቻቸትና ስፖንሰሮችን ማቅረብም የስራዋ ድርሻ ውስጥ አንደኛው በመሆን ከፍ ያለ ገቢን መፍጥር መሆን ሲገባ፣ ለጩልሌዎቹ ይህንን በሕብረተሰቡ ስም እንዲተገብሩና የግል ጥቅም እንዲያገኙ የማህበሩን ስምና ማህተም እያመቻቹ የእውቅናና የትብብር ጥያቄ ደብዳቤ አዘጋጂ ባልተሆነ ነበር። አሁን ደግሞ የተሰገሰጉትና የምርጫ አገልግሎት ጊዜ የተቃጠለባቸው፤ የሕብረተሰቡ ንቃት ስላስፈራቸው፤ ባለፈው 2 አመት ከሰሩት አስነዋሪ ተግባር ላለመጠየቅ ሲሉ፣ ሕብረተሰቡ ባልመከረበት ፣ ባልሰጣቸውም ሥልጣን መተዳደሪያ ደንቡን በአንባገነንነት ለውጠው ትረስቲ አቋቁመናልና መርቁልን ብለው አይናቸውን በጥሬ ጨው አጥበውና አፍጠው እንዲሁም አግጠው መምጣታቸውን ባለፈው ጥሁፋችን እንዲሁ አስረግጠን ማቅረባችን እሙን ነው።
እንግዲህ ለእነርሱም እንደ ቀኝ እጅ የሚጠቀሙበትስ የሬዲዮ ፕሮግራም ተመሳሳይ የቅጥረኛ ተግባሩን ከማካሄድና የግለስቦች የግል መጠቀሚያ ከመሆን ወጥቶ መቼ ነው ለሕብረተሰባችን የሚጠቅም በሚሆን መልኩ ብቃት ባላቸው ሙያተኞችና በማህበሩ በቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ሥር መዋል የሚችለው? አሁንማ ሠርጌን ወይንም የጋብቻና የልደት በዐሌን በመረዳጃ ራዲዮ እንዲያበስርልኝ እከሌን ልጥራው፤ የሚዘግቡትን ስለማያውቁ ከኢንተርኔት ብቻ የከረመውን ዜና እንዳለ ኮፒ እያደረጉ ማቅረብን እንደ አገልግሎት የሚቆጥሩ፤ ወዘተ….. ብለን ድክመታቸውን ብቻ ሳይሆን ማይክ ስለያዙ ብቻ ለሕብረተሰቡ የሚበጀውን፣ አንድነቱንና ሕብረቱን በመጠቀም ከውስጡና ከውጪ የሚገኙትን ሙያተኞች በማስተባበር፤ ሕብረተሰቡ ትምህርት ያገኝበታል፣ እውቀቱን ያሻሽልበታል፣ በመተባበርና አንድ ሆኖ በመረዳዳት ኑሮውን ያሻሽልበታል፤ ከዚህ ሀገር ኑሮና ባሕል ጋር እንዴት ሊጣጣም ይችላል፤ ወዘተ በመሳሰሉት ነጥቦች ላይ በቂ ግንዛቤን ይጨብጥበታል የተባሉ ጊዜያዊ ሆነ ዘለቄታው ፕሮግራሞችን በመንደፍ ማቅረብ ተገቢ ነው።
የሙያ አድማሶቻቸው የሰፉ ማለትም ከፍተኛ የትምህርትና የሙያ ብስለታቸውን አጣምረው የተቀመጡት የኢትዮጵያ ተወላጆችም ቢሆኑ እራሳቸውን በማዘጋጀት ለሕብረተሰባችን ሊሰጡት የሚችሉትን አስተዋጾ በቀላል የሚገመት አይድለምና ከየጓዳው በመውጣት ያለምንም ይሉኝታ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ እያስገነዘብን፤ አንዳንድ ጠባብና የግል ጥቅም ያሰከራቸው መንገዱን አስቸጋሪ ሊያደርጉባቸው እንደሚሞክሩ ያለፈው ተመኩሮዎች ቢያስረዱም፤ ፍላጎቱና ቅንነቱ እስካለ ድረስ “ይቻላል“ እንደተባለው ለውጤት እንደምትበቁ በመተማመን ነው። የኢትዮጵያ ተወላጅ ካልሆኑት ያላችሁም net work ቀላል ስላልሆነ የውጪዎችንም በየፈርጅ አሰባስቦ ጠቃሚ የሆኑና ሕብረተሰባችንን ሊያሳድጉ የሚችሉ ድንቅዬ ሥራዎችን በተግባር እንደምታውሉ እርግጠኞች ነን።
እርሶስ ምን ይላሉ?
No comments:
Post a Comment