Friday, April 8, 2011

የሀሰት ተቃዋሚና ያገኘው ጣጣ!

የርሶ ብዕር አስተያየት ተሳትፎ ሕብረተሰባችንን ይጠቅማል ያሉትን አይንፈጉን ገንቢነቱ ቦታ ይኖረዋልና! 

ማሳሰቢያ፡ ይህ ገጽ የተዘጋጀው የተለያዩ የኅብረተሰባችንን ሀሳብ ለመለዋወጫ እንጂ ለሚሰጡት ማንኛውም አስታየቶች በማንኛውም መንገድ ተጠያቂ አይደለም። ጉግል ድርጅትም ኃላፊነት አይወስድም። ኃላፊነቱ በሙሉ የአስታየት ሰጪው ብቻ ነው።


የሀሰት ተቃዋሚና ያገኘው ጣጣ!

አቤቱ ፈጣሪያችን ሆይ! ለዚህ ጊዜና ሰአት ፈቃድህ ሆኖ ከሩቅ ላሉት ወዳጆቻችን በዚህ ገጽ አማካኝነት እንድንገናኝ ላደረከው ለቅዱስ ስምህ ክብርና ምስጋና ይሁን። የተውደዳችሁ የዳላስ እድምተኞቻችን እኛ በመዳህኒዓለም ጸጋ በያለንበት ሰላም ነን።

የቅዱስ ሚካኤልም ደብር ድንቅና ውብ እያደረገ አገልግሎቱን እያበረከተ ለመሆኑ ከስፍራው የሚደርሰን መሆኑን እያስረገጥን በተለይም የሚካኤል ሠይፍ አባላትም እየተጠናከሩ ይገኛል። በአስተዳደር ቦርድ ውስጥ ፖለቲከኞች ያሰረጉትና ባለፈው አመት በጠሀፊነት ያገለገለውን አበበ ንጋቱን ጊዜው አሁን ነውና ከሀላፊነቱ እራሱን እንዲያገል ግፊት ጀምረዋልና ሀሳባቸውን እኛም እንጋራዋለን። ካልሆነም በመጪው ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ተነስቶ ፣ እንዲለቅ መደረጉ አይቀሬ ነውና። ሌላው አንዳንድ አዛውንት አይባሉ ወይ በሰላም የማይቀመጡ ጡረተኞች ከማንም በላይ በጡረታ ገቢ እያገኙ ነገር ግን ከደብሩ የአባልነት መዋጮ ከ5 ዶላር በላይ መክፈል ያልፈለጉ፣ እንዲያውም ቆራቢ ነን እያሉ የለየላቸው ዋሾ ሌላው ሁሉ ቢከሽፍባቸው፤ ዛሬ ደግሞ እንደ ለመዱት ቄስ የማነ የተባለውን ቅጠሩት የሚል ዘመቻ ከፍተዋል አሉ። ከዚህ በፊት ቦርዱ የክፍት ሥራ ቦታ ማስታወቂያ አውጥቶ በነበረበት ወቅት መስፈርቱን ባለሟሟላት ሊቀጠር አልቻለም። የጠመጠመ ሁሉ አንድ እንዳልሆነ ሁሉ አሁንም ሚካኤል ደብር እንደ ወጣቱ ዲያቆን ያሉትን እጅግ የላቁና ከፍተኛ ግልጋሎት መስጠትና ችሎታቸውን በመተግበር ያረጋገጡትን ፤ ደብሩንና ምዕመኑን ብቻ ሳይሆን ተረካቢውንም ትውልድ አንጸው የሚይዙትን ዛሬም ይፈልጋል። ዕድሉ ቢጠብ እንኳን ባሉት ይተካል። ያ ነው የአስተዳደሩ ሀለፊነት፣ ደብሩን ማሳደግና መጠበቅ፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ መተግበር፤ ለምዕመኑ የሚያስፈልገውን ተገቢ ግልጋሎት በሰፊው እንዲቀርብ ማድረግና ማረጋገጥ፤ ብቁ የሆኑ አገልግሎቶችና አገልጋዮችን መተግበር ማረጋገጥ እንጂ ሥራአጥ ጡረተኞችን እሽሩሩ ማለትን አይደለም።

በሊላው በኩል በትውልድ ሀገራችን ከምርጫ 97 በኃላ ምንም አይነት ሀቀኛ የተቃዋሚ ጎራ አለ ለማለት እየታወክን ባለንበት ወቅት ፣ የገዢው አካል ጭፍሮቹን በ16 የሰሚን አሜሪካና በ2 የኢሮፕ ከተሞች የሰደደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 14 በአሜሪካን ግዛት ሲሆን አንደኛው በናንተ በዳላስ ከተማ እንደሚሆን ቀደም ብለን መዘገባችን እሙን ነው። ተቃዋሚ ነን ባዮች የራሳቸውን ስብሰባ እንደሚከውኑ ሁሉ ገዢውም ዲሞክራሲ ባለበት ሀገረ አማሪካ ቢለማመደው ትምህርትን ያገኝበት ይሆናል ለማለት ባንዳዳም፤ እንደምንሰማው ከሆነ ግን ለታላቁ ሚሊኒየም ለተባለው የአባይ ሀይል ማመንጫ ግድብ የሚሆን ንዋይ አሰሳ ነው ስለተባለ ፤ ይህንኑ እውን ለማድረግ መረዳዳቱ አይከፋም። ነገር ግን በግል ጥሪ ብቻ የሚደረገውን ስብሰባ እኛም ሆን ገጻችን እንኮንነዋለን። ብልህና አስተዋይ አመራሮች ቢኖሩ ኖሮ ማንኛውም የኢትዮጵያ ተወላጅ ሁሉ እንዲካፈል በማድረግ በሩን ሲከፍቱ፤ ምን አልባትም የደህንነት ችግር ጥርጣሬ ካለ፣ እያንዳንዱ ተሳታፊ መታወቂያውን እያስመዘገበ እንዲሳተፍና የሕግ አስከባሪውም ሕግን እንዲያስከብር ማድረግ በተገባ። የመንግሥት ተወካዮችና ደጋፊዎቻቸው በስብሰባው ላይ የተጠቀሙበትን እኩይ ሰአትም ለተቃዋሚ ዕድል በመስጠት እንዲተነፍስና ሁሉም ወገን የየራሱን ግንዛቤ እንዲጨብጥ መድረክ ማዘጋጀቱ በተገባ ነበር።

በሌላ በኩል የድርጅት ሥም ብቻ ያነገቡና ከወጣትነታቸው ዘመን ጀምሮ የተቆራኛቸው በሽታ ቢኖር የአዲስ አበባ ቤተመንግስት እንጂ የጊዜው የፓለቲካ ትግል ስልት ያልቃኛቸው፤ ከወጣትነታቸው ዕድሜ ብረት አንስተው ኃይልና ደም መፋሰስን የሚያውጁ፣ አንዴ ኢሕአፓ፣ ሲፈልጉ ቅንጅት፣ ወዘተ,,,,,, አሁን ደግሞ በቃና ወዘተ እያሉ ንጹሀንን ደም እንዲፈስ የሚቋምጡ፣ ትላንት እሰየ አብርሃ የተባለውን የትግራይ ነጻ አውጪ ከፍተኛ ሀላፊና ሀገር አስገንጣይ እንዲሁም በንጹሀን ደም ተጠያቂ ጋር የገጠሙ፤ ኸረ ስንቱን እንበል፤ ነፍሰ ገዳይ ሁሉ በኮበለለ ቁጥር አንድ ከሆነ እንግዲህ ነገ መለስ ዜናዊ ሮጦ ቢወጣ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው የሚቀበሉ ጉዶች ሁሉ፤ ዛሬም የኢትዮጵያ ጠላትነታቸውንና የህብረት አፍራሽንነታቸውን ባላቸው የግል ጥቅም ምክንያት እንጂ ከዚያ የዘለለ የላቸውም። ትምህርት የሌላቸውም ሆነ የሚያድሩበት ሙያ አልጠቅም ወይ አልጠግብ ብሏቸው አሊያም ክፉ በሽታ የሆነባቸው ናቸው። እንጀራ መጋገሩም ሙያ ሊሞዚን መሾፈሩም ሙያ፣ ሌላውም እንደዚያው ነገር ግን ሁከትና ጥላቻ መፍጠር ሳይሆን አንድ ሆኖ ተቀምጦ በውይይት መስተናገድን አንቀበል ብለው እስከ ሆቴል አስተዳደር ድረስ በመቅረብ ኃይል የተሞላበት ማስፈራራት ማድረግና የሆቴሉን ተስተናጋጆች ደህንነትን ጥያቄ ላይ ማድረስ ሕገ ወጥ ብቻ ሳይሆን ተያይዞ የሚያስከትለው ጣጣ በሽብርተኝነት መጠየቅም ጭምር ነው።

እንግዲህ ይህን የሚተገብር ወይንም የሚያስተገብር ህሊና ጨብጦ ነው ላገር መቆርቆር? ይህ አሲምባ ወይንም የኢትዮጵያ ጫካ አይደለምና ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም። በተለይም የ ዲኤፍ ደብልዩ ኢትዮጵያ ገጽ ወይዘሮ የጠቀሷቸው ግለስቦችን የኛም ገጽ ይጋራቸዋል። ወደ ዳላስ የመጣውም ቡድን ከፈለገው ወገን ጋር በጋራም ሆነ በተናጠል የመገናኘት መብቱን ብንጠብቅም፤ ከላይ እንደጠቆምነው በሩን ለሁሉም ክፍት ቢያደርገውና ሁሉንም ቢያስተናግድ መልካም መሆኑን ደግመን ልናስገነዝብ እንፈልጋለን።

የዳላሱን መረዳጃ ማህበርን አሻፈረኝ አንለቅም ያሉትን የዳላሱ ሕብረተሰብ በተባበረ ሀይሉ ማንሳትና ይሆኑኛል ባላቸው መለወጥ ይገባዋል። ስለዚህ ጉዳይ ባለፉት መጣጥፎቻችን ብዙ ዘግበነዋልና አንመለስበትም። የውጤቱ ቀማሾች ዳላሶች ብቻ ናችሁና መልካሙን ሁሉ እንመኝላችኃለን። መልካም የትንሳኤ በአል ይሁንላችሁ።

እርሶስ ምን ይላሉ?

No comments: