Friday, September 24, 2010

ከአብራካችን ለወጡት ልጆቻችን ምን እየተውን ነን?

የርሶ ብዕር አስተያየት ተሳትፎ ሕብረተሰባችንን ይጠቅማል ያሉትን አይንፈጉን ገንቢነቱ ቦታ ይኖረዋልና!


 ማሳሰቢያ፡ ይህ ገጽ የተዘጋጀው የተለያዩ የኅብረተሰባችንን ሀሳብ ለመለዋወጫ እንጂ ለሚሰጡት ማንኛውም አስታየቶች በማንኛውም መንገድ ተጠያቂ አይደለም። ጉግል ድርጅትም ኃላፊነት አይወስድም። ኃላፊነቱ በሙሉ የአስታየት ሰጪው ብቻ ነው።



ከአብራካችን ለወጡት ልጆቻችን ምን እየተውን ነን?

ዛሬም እንደ ድሮው ፣ ዘመን ከዘመን ሲለወጥ፣ የአምሮ እድገትና ብስለት ያልታደሉ፤ በአዲሱም አመት አዲስ መንፈስና አስተሳሰብ የጎደላቸው፤ ዘንድሮም ዝጎ በኖረ አእምሯአቸው የሚተፋውን የገጻቸውን ጥሑፍ ከጎናቸው እየተለዩ የሚገኙትን ጆሮ ቆራጭ መጣባችሁ በማለት ያምናውን ለዘንድሮ ማስፈራሪያ ሊያደርጉ ይዳክራሉ። ካለፈው ተምሮና ተጸጽቶ ማንነታቸውን ሲያውቅና እውነተኛውን መንገድ ሲመርጥ፣ እንዴት ትላንት ሲተቹህ ከነበሩ ጋር ተስማማህ? እየከዳኸን ነውን? አምና ባደባባይ ላሉህ እውነት እንደው ይቅርታ እንኳ ሳይሉህ? የሚለውን ገጻቸውን አይተን እናንተንም እውነቱ ይገለጽላቹ፣ ይሳካ ዘንድም እንጸልይላችኃለን ነው የምንል። የተወደዳችሁና የገጻችን አንባቢዎች እንዴት አላችሁልን? ፈጣሪ ሁላችንን በመንፈሱ ይምራን ይጠብቀን! የራቁንንም መክሮና አስተምሮ ወደእውነተኛው መንፈስ ይቀላቅላቸው ! አሜን።

ወደ እርዕሳችን ስንመለስ፤ ብዙዎቻችን ወደንም ሆነ ተገደን አሊያም ምርጫ በማጣት ከወላጆቻችን ወይም ካሳደጉን ፈቃድ ሆኖ የቀለም ትምህርት የጀመርነው ከቄስ ትምህርት ቤት ነበር። ፊደል ቆጥረን ወንጌል አንበን ዳዊት ደግመን የተመርጡ ወደ ድቁና ብለውም ወደ ከፍ ያለው መንፈሳዊ አገልግሎት ሌላውም ወደ ዘመናዊ ትምህርት የቀጠሉበትን ስናወሳ፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ እምነትን አብረን ይዘነው አድገናል። ከዚሁ ጋር እንደ ኑሯችንና አመለካከታችን ዕምነቱን መተግበሩ ላይ በተለያየ ደረጃ ላይ ተቀምጠናል። አንዱ ሲያጠብቀው ሌላው ሲያላላው ክዚህ ደርሰናል። በተለይም በምዕራቡ ዐለም የምንኖር ደግሞ ባለፈው ፴ አመት ውስጥ በተለያየ ምክንያቶች ከአገር ከወጣን ጀምሮ ያለብንን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማርካትና የፖለቲካውን እንቅስቃሴ ለሚያኬሄዱትም የጥሩ መገናኛ አጋዥ መድረክ በመክፈቱ ወቅታዊ ድጋፍን አስመዝግቦ በብዛት ኢትዮጵያዊያን በሰፈሩበት ትላልቅ ከተሞች መመስረትን ጀመሩ። በ፩፱፻፺ዎቹ ውስጥ በሀገር ቤቱ የመንግሥት ለውጥ በኃላ በአንዳንድ ቤተ ክርስትያኖች ውስጥ በዘርና በፖለቲካ  ብሎም ምዝበራን በተመለከተ አንዳንድ ክስተቶች ቢፈጠሩም ሀይማኖቱ ቀጣይነቱን እንዲሁም እምነቱ ያላቸው አዲስ መጤ ቁጥር ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ የቤተ ክርስትያን ቁጥሩ እየበዛ መጥቷል። በተለይም ቀሳውስቱ ቤተ ክርስትያኑን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለአሃዙ ማደግ አስተውጾ አድርጓል።

እዚህ ላይ መዝለል የማንችለው ራሱን ማኅበረ ቅዱሳን እያለ የሚጠራው የቤተ ክርስትያናችን በቀል የሆነው ቡድን በአንዳንድ ከተሞች የናንተን ዳላስ ሚካኤልን ጨምሮ ፖለቲካንና ስራውን ከቤተ ክርስትያን አካባቢ አጥፍቶታል ወይንም እንዲቀንስ ከፍተኛን አስተዋጾ አበርክቷል። በሌላ በኩል ይኸው ድርጅት ፖለቲከኞችን አመለካከት ቢያስለውጥም በአንጻሩ ወደ ቤተ ክርስትያኖች አመራርና ካዝና ምዝበራ ወይንም አክራሪ በሆነ ደረጃ ችግሮችን እየከሰተ ይገኛል። ልጆቻቸውንም ወደዚሁ ከራራ አስተሳሰብ እያስገቧቸው ይገኛል።

ሌላው መከፋፈልን በምዕራቡ አህጉር ያመጣው የአባቶች አልመግባባትና መለያየት ነው። ይኽ አደገኛ አዝማሚያ በቅርቡ ካልተቋጨ ቤተ ክርስትያኗን ወደ መከፋፈል ያደርሳል ብለን እንሰጋለን። ለምሳሌ ለማገናዘቢያ ብቻ እንጂ እንደማወዳደር እንዳይወሰድብን የምንጠቅሰው በሱኒና በሻይት የእስልምና ተከታዮች ጉዳይን ነው። እኛ አንድ ሀይማኖትና አንድ እምነት ተከታዮች የሆንንና በሰለጠነው ዓለም የምንኖር በሁለት ሲኖዶስ ለምን እንለያያለን?  ቤተ ክርስትያን ስናቋቁም እርስ በራሳችን ተረዳድተን ለብቻችን አልነበረምን? ሀገር ቤት የነበረው ሲኖዶስ ምንስ የረዳን ነበር? ቀሳውስትስ ለማምጣት ምን አይነት ችግር ነበረብን? ዛሬ ግን ይህንን ጽዋ የቀመሱም ሆነ ያልቀመሱ፣ ዛሬ የተመቻቹ ወይንም የተለየ ፍላጎት ያደረባቸው ግለሰቦች ያለ አባት ቤተ ክርስትያን እንዴት ይከፈታል ይሉናል። ጥያቄውን ብንቀበልም ባለው ያባቶች ልዩነት ከየትኛውም ላለመሆን የመረጡትን ለምን ያዋክቧቸውል? ለመሆኑ ትላንት እንዴት አብረው ያለ ሲኖዶስ እውቅና አብረውን ቤተ ክርስትያን ከፈቱ? ትላንት ያለ ስልጣናቸው ከተሰጣቸው ሀላፊነት እንደዚሁም አስተዳደር ረግጠው (በስደት ስም) የወጡ አባቶች አልነበሩምን ከከተማ ወደ ከተማ እየተዘዋወሩ የምዕራቡን ሀገር ነወሪ ለሆኑት የእምነቱ ተከታዮች ለሚመሰርቱት ቤተ ክርስትያን የሚባርኩ? ሕጉንና ስረአቱን አፍርሰው ከተመደቡበት ሀገር ለቀውና የፓለቲካ ስደተኛ መሆን ምንድን ነው? ሲሆን ወደ ገዳም ገብቶ የሚያስፈልገውን መወጣትን እንዴት አጡት? እንደ አ. አ. የ፹ ዎቹ ስደተኛ በ፺ኛው ዓ.ም.   ተራ ደርሷቸው  የልዑል ፈጣሪም ዝምታ ይሁን ፈቃድ አመራሩን የያዙትም ቢሆኑ የነገሩ ጀማሪያት የሚደመሩ መሆናቸውን እንዴት መገንዘብ ይሳናል?

እኛ ተራ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ያለእኛ ወይንም ተከታይ የሌለው እምነት እድሜው እንደሚያጥር ሁሉ፤ አባቶችም ወደ አባትነት ለመብቃት ብቻ ሳይሆን ወደዚያ የመሰለ መንፈሳዊ አገልግሎት መግባት በርሱ የመመረጥና የመቀባትን እድል እንደሆነና ብጹህ ተብሎ ለመጠራት ይቅርና የቄስን ቅስናውንም እንዳይጠይቅ ሲነገረን እንዳልኖርን፤ ዛሬ የምን ቁጣ ነው በላያችን የተሸከምነው? የበጉ እረኛ የተመረጡ ብለን ስንቀበላቸው ፣ ከነሱ ብዙ መማር ሲገባን፣ እነሱን ሀዘናችንን አስወጋጅ፣ለቅሶዎቻችንን ኣባሽ ፣ ጥፋታችንንም ሆነ የመንፈስ መታወካችንን ይዘን ወደ ነሱ ስንጠጋ ሀኪሞቻችን፣ ባጠቃላይ የስጋና የመንፈስ ሕይወታችንን የሚያስተካክሉ ብለን የተቀበልናቸው፣ እኛ እነርሱንም ፈጣሪንም አክብረንና ፈርተን የቤተክርስትያናችን ሁኔታ እያሳሰበን የነሱ አለመግባባት ለኛም እየተረፈን በመካከላችን አለመጣጣምን እያጎላ መጥቷል። አንዳንዶችንም እምነትና አመለካከትን እንዲለውጡ እስከማድረግ በቅቷልና ይህንን የጀመረንን በምዕራቡ ሀገር የምንገኝ የእምነቱ ተከታዮች የሆንን በጥልቅ የማጤንና የጋራ የሆነ አንድዮሽ መንገድ ለመፍጠር ልዩነታችንን በቀና መንፈስ መፍታት አማራጭ የሌለው የወቅቱ ጥያቄ አድርገን በመውሰድ ዛሬውኑ እልባት ማግኘት የሚገባን ወቅታዊ ጥያቄ ነው።

ማሳሰቢያ ፣- የዚሁ አርዕስት ቀጣይ በሚቀጥለው ጥሁፋችን ይጠብቁ።

No comments: