ማሳሰቢያ፡ ይህ ገጽ የተዘጋጀው የተለያዩ የኅብረተሰባችንን ሀሳብ ለመለዋወጫ እንጂ ለሚሰጡት ማንኛውም አስታየቶች በማንኛውም መንገድ ተጠያቂ አይደለም። ጉግል ድርጅትም ኃላፊነት አይወስድም። ኃላፊነቱ በሙሉ የአስታየት ሰጪው ብቻ ነው።
ከዚህ በታች ያለውን ጽሑፍ ያገኘነው ሪፓርተር ተብሎ ከሚጠራው ድህረ ገጽ ላይ ሲሆን ምናልባት እድሉን ላላገኙት በዚህ አጋጣሚ አንብበው እንዲዝናኑና ግንዛቤ እንዲጨብጡ ነው።
ክቡር ሚኒስትር
WEDNESDAY, 23 JUNE 2010 10:03
User Rating: / 3
PoorBest
- እናንተ ፀሐፊዎች ስትባሉ አንዳንድ ጊዜ ከሚኒስትር በላይ ካልሆን ትላላችሁ፡፡ እኔ በጧት ስገባ፣ አንቺ አሁን ትገቢያለሽ?
- ውይ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ ዝናቡ በጭራሽ ከቤት አላስወጣ አለኝ፤ ታክሲ ድረስ እንዴት ልሂድ... ዝናቡ... የዛሬ ጧቱ ደግሞ ልዩ ነው፡፡
- ለነገሩ እውነትሽን ነው - የዛሬ ጧቱ ዝናብ እኔም ገርሞኛል፡፡ አንዳንዴም ያስፈራኛል፡፡ - ዝናብ ፀጋ ነው እንጂ ምን የሚያስፈራ ነገር አለው ክቡር ሚኒስትር?
- በጋውንም፣ ክረምቱንም እንደዚህ ተደበላልቆ ዝናብ ብቻ ሲሆን፣ ፈጣሪ ባጀቴን ጨርሼአለሁ ብሎ በዋናው ተፈላጊ ጊዜ ዝናብ የለም እንዳይለን ነዋ"
- አያስቡ ክቡር ሚኒስትር... ፈጣሪ በኢትዮጵያ አይጨክንም፡፡ እግዚአብሔር ራሱ የሚኖረውስ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደል?
- ደግሞ እንዲህ ማለት ጀመራችሁ? በሉዋ ብላችሁ ብላችሁ ለፈጣሪም የቀበሌ መታወቂያ ስጡታ ሆ"ሆ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚኖረው አላችሁ?
- ቀልዱን አልሰሙም መሰለኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን የሚሉት ቀልድ?
- ልንገርዎት?
- ንገሪኝ፡፡
- "ሰውዬው ጃፓን አገር ሄዶ አንድ ልዩ ሞባይል ያይና ዋጋውን ሲጠይቅ አንድ መቶ ሺሕ ዶላር ይሉታል፡፡ ለምን ይህን ያህል ውድ ሆነ ብሎ ሲጠይቅ ሞባይሉ ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ያገናኛል ያነጋግራል ይሉታል፤"
- እሺ - ሆ...ሆ...
- "ውድ ነው ብሎ ይተወውና ቻይና አገር ሲሄድ ይህንኑ ሞባይል ያይና ዋጋ ሲጠይቅ እንደ ጃፓኑ መቶ ሺ ዶላር ይሉታል፡፡ ምክንያት ሲጠይቅ እንደ ጃፓኑ ከፈጣሪ ጋር በቀጥታ ስለሚያነጋግር ነው ብለው ይመልሱለታል፣"
- እሺ!
- "ዱባይ ሄዶ ይጠይቃል፤ ተመሳሳዩ ሞባይል ተመሳሳይ የአንድ መቶ ሺ ዶላር ዋጋ እንዳለው ይነግሩታል፡፡ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ስለሚያነጋግር ነው ይሉታል፤"
- እሺ ሆ...ሆ
- "ዋጋው ውድ ነው ብሎ ሌላ ሥራውን ሠርቶ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል፤"
- እሺ!
- " ኢትዮጵያ ውስጥ ያቺን ሞባይል ያያታል፡፡ ዋጋው ስንት ነው? ብሎ ይጠይቃል፡፡
- እሺ!
- "አንድ መቶ ብር ብለው ይመልሱለታል፤"
- እሺ!
- "ይህ ሞባይል በሌሎች አገሮች ከፈጣሪ ጋር በቀጥታ ያነጋግራል፤ እኛ አገር ግን አያነጋግርም? አያገናኝም ወይ? ብሎ ይጠይቃል፤"
- እሺ!
- "ታዲያ ከፈጣሪ ጋር የሚያነጋግር ከሆነ ውጭ አገር አንድ መቶ ሺ ዶላር እያወጣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ መቶ ብር ብቻ ለምን ይሆናል? ብሎ ሰውዬው አሁንም በመገረም ይጠይቃል፤"
- እሺ!
- "ፈጣሪነኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚኖረው፤" ብለው ይመልሱለታል፡፡
- እ... ምን አለ?
- "ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖርስ ከሞባይል ዋጋ ልዩነት ጋር ምን አገናኘው?" ብሎ ሲጠይቅ፡፡
- ምን ብለው መለሱለት?
- "እንደ ፣ሎካል ኮል፣ ነው የሚታሰበው፤"
- ሃ...ሃ...ሃ ቀልዳችሁ ግሩም ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እንደናንተ አባባል ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረ እያለም አገራችን በድርቅና በረሃብ እንደምትጠቃ አትርሱ፡፡
- ነው ግን ክቡር ሚኒስትር አንድ ነገር አይርሱ "ሎካል ኮል" ማለትነኮ "ጥሪ አይቀበልም" የሚል መልስ አይኖርም ማለት አይደለም፡፡
- በይ፣ በይ ቀልድሽን አቁሚና ትናንት የሰጠሁሽን ፅሑፍ በአስር ኮፒ ለአሁን አዘጋጅልኝ፡፡ ለስብሰባ እፈልገዋለሁ፡፡
(ለስብሰባ የሚያስፈልጓቸውን ኮፒዎች እንደያዙ ከቢሯቸው ሊወጡ ሲሉ ፀሐፊዋ ፈቃድ ጠየቀቻቸው)
- የት ለመሄድ ነው ፈቃድ የምትጠይቂው?
- ክቡር ሚኒስትር ልጆቼ ወደሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመሔድ ፈልጌአለሁ፡፡
- አስቸኳይ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ትምህርት ቤቱ ቀስ በቀስ እየተበላሸ በመሔዱ ችግሩ ምንድንነው ብዬ ለማነጋገር እፈልጋለሁ፡፡
- ተበላሸ ስትይ?
- ገና ሲጀመር ወላጆችን በደንብ ያነጋግሩ ነበር፡፡ የወላጅ ሐሳብ ያዳምጡ ነበር፣ ደህና ደህና አስተማሪዎች ይቀጥሩ ነበር፣ መፅሐፍት ነበር፣ ዋጋው ጥሩ ነበር፣ አሁን ገንዘብ ክፈሉ ብቻ ነው፡፡ ንቀትና እብሪት ያሳያሉ፣ ስትጠይቃቸው ለምን አትተውትም ይላሉ፣ በየጊዜው ማስጠንቀቂያ ማውጣት ነው፡፡ ለመፅሐፍት፣ ለሌላ ሌላውም በየጊዜው ጭማሪ ማስከፈል ነው፡፡
- ያ በቀደም የነገርሽኝ ትምህርት ቤት ነው?
- አዎን፡፡
- የእህቴ ልጆችነኮ እዛ ነው የሚማሩት፤ እውነት እንዳልሽው ከሆነማ እህቴን ልጆችዋን ከትምህርት ቤቱ እንድታስወጣ እነግራታለሁ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር እርስዎም እንደኛ ሆኑ እንዴ?
- እንዴት እንደኛ ሆኑ እንዴ - አልገባኝም?
- ክቡር ሚኒስትር በእርስዎ ደረጃ መደረግ ያለበትማ ለትምህርት ሚኒስቴር ነግሮ ትምህርት ቤቶች በተፈቀደላቸው የሥራ ፈቃድና በተሟላ አቅም እየሠሩ መሆናቸውን ቁጥጥር እንዲደረግ ማድረግ ነው፡፡
- እኛም ወላጆች እናንተም ወላጆች ምን ልዩነት አለን?
- እናንተ ባለሥልጣን ኃላፊነት የተሸከማችሁ፣ መመሪያና ሕግ በማውጣት ትልቅ ሚና የምትጫወቱ ናችሁ፤ እኛ ተራ ነን፡፡ እኛ ብናኮርፍ ያምርብናል፡፡
- እኛስ?
- እናንተ ዕርምጃ እንዲወሰድና እንዲስተካከል ታደርጋላችሁ፡፡
- እህም በይ አሁን ወደ ስብሰባ ልሔድ ስለሆነ አብሮኝ እንዲሔድ የፕላኒንግ ኃላፊውን ጥሪልኝ፡፡
- ችግር አጋጥሞት አልመጣም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ችግር አጋጠመው?
- ልጁ ታሞ አንድ ሆስፒታል ሲወስደው ሆስፒታሉ አደገኛ በሽታ እንደያዘው ነገረውና ወደ ሌላ ሆስፒታል ሄዶ ልጁን እያስመረመረ ነው፡፡
- ትቀልጃለሽ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር በጣም ተጨንቋል፤ እንዲያው በጣም በጣም ተቸግሯል፤ እንዲያውም ደውለው ቢጠይቁት ጥሩ ነው፡፡
- (ሞባይላቸውን አወጡና ደወሉ) ሃሎ!
- አቤት ክቡር ሚኒስትር (የፕላኒንግ ኃላፊው)
- ልጅህ መታመሙንና ሆስፒታል እንዳለህ ፀሐፊዬ ነግራኝ ነው፡፡
- አዎን ክቡር ሚኒስትር ሆስፒታል ነው ያለሁት፤ ስለጠየቁኝ አመሰግናለሁ፡፡
- የልጅህ ሁኔታ እንዴት ነው አሁን?
- ሰሞኑን በጣም ደንግጨና ተስፋ ቆርጨ ነበር፡፡ አንድ ሆስፒታል ሄጄ አደገኛ በሽታ ነው ብለውኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ሌላ ሆስፒታል ሄጀ ሳስመረምረው የመጀመሪያው ዶክተር ያለው ስህተት ነው፤ አደገኛ በሽታ አልያዘውም ብለውኛል፡፡
- የትኛው ሆስፒታል ነው አደገኛ ነው ያለህ?
- እዛ ቢሮአችን አጠገብ ያለው፡፡
- እንኳን ነገርከኝ፤ ሁለተኛ ልጆቼን ወደዛ ሆስፒታል አልወስድም፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር እርሶማ እንደዛ ሊሉ አይችሉም፡፡
- ለምን አልችልም? አንተ ራስህ መጥፎ ሐኪም ያለበት ሆስፒታል ነው ብለኸኝ የለም ወይ?
- አዎን ብያለሁ ግን እኔ ሌላ ለማለት አቅም የለኝም፡፡
- እኔስ?
- እርስዎማ ክቡር ሚኒስትር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደውለው ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እንዲኖር፣ የሙያ ሥነ ምግባርም በሐኪሞች እንዲዳብር መጫን፣ መመሪያና ሕግ ማውጣት ይችላሉ፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ጋር መመካከር ይችላሉ፣ ሐሳብ ማቅረብ ይችላሉ፡፡
- ልዩነት አለን እያልከኝ ነው?
- አዎን ተራ ሕዝብ ሌላ፣ ባለሥልጣን ሌላ፡፡
- ሕዝብ ወሳኝ ነው የሚለው ዕምነትህ ተለወጠ ማለት ነው?
- ሕዝብ ወሳኝ የሚሆነው አመራር ሲያገኝ ነው፡፡ ምሩ እንመራለን እያልኩ ነኝ፡፡
- በል ገባኝ በበሽታ ላይ በሽታ አልጨምርብህም ችግር ካለ ደውልልኝ፡፡
- አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቻው፡፡
(ክቡር ሚኒስትሩ ስብሰባ ውለው ደክሟቸው ወደቤታቸው ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ይጓዛሉ)
- እንዴ ወዴት ወዴት ነው እየነዳህ ያለኸው?
- አውቄ ነው ክቡር ሚኒስትር፣ በዛኛው መንገድ ቅድም ልከውኝ ስሔድ አይቼው ነበር፣ ቤት መግባት አንችልም፡፡
- ምን አጋጠመ?
- ትልቁ ቧንቧ ፈንድቶ መንገዱ በውኃ ተጥለቅልቋል፤ የመብራት ኃይል ምሰሶዎች ወድቀው የሚያነሳቸው አጥተዋል፡፡ ብቻ አካባቢው "ሱናሚ" ያጠቃው ነው የሚመስለው፡፡
- ትቀልዳለህ?
- እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ኧረ እንኳን ነገርከኝ - መኪናውን ስይዝ ሁለተኛ በዛ አልሔድም፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን እንዴ?
- እርስዎማ እንደኛ እንደዛ አይሉም፡፡
- ለምን አልልም?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር እርሶማ ወደ ውኃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤት ደውለው፣ ወደ መብራት ኃይል ደውለው እንዲጠግኑና እንዲያስተካክሉ ይነግራሉ እንጂ፣ እንደኛ አኩርፈውና ተናደው በዛ አልሔድም ይላሉ እንዴ?
- ለምን አልልም፣ አንተ ብለህ የለም ወይ?
- መሪ ሌላ፣ ተመሪ ሌላ፡፡
- መሪውን የጨበጥከው አንተ ነህ፡፡
- ግዑዝ ነገርን የሚመራ ሌላ፣ ሕዝብን የሚመራ ሌላ፡፡
(ክቡር ሚኒስትር መሸትሸት ብሎ ቤት ገቡ፤ ሹፌሩም ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ወሬው ከባለቤታቸው ጋር ነው፤ የዓለም የእግር ኳስ ውድድር እያዩ)
- እሺ ማን እየመራ ነው? (ክቡር ሚኒስትር)
- ፓርቹጋል 7 ሰሜን ኮሪያ ዜሮ፡፡
- ምነው፣ ምነው ሰሜን ኮሪያ፣ በስህተት የዋና ቡድን ልኮ እንዳይሆን?
- መቀለድህ ነው ከእኛ ይሻላሉ፡፡
- የእኛ አገር እግር ኳስማ እንኳን ላየው ስለሱ ሲወራም ያቅለሸልሸኛል፡፡
- አንተማ እንደዛ ልትል አትችልም፡፡
- እንዴት አልችልም?
- አንተነኮ ክቡር ሚኒስትር የተከበሩ ሚኒስትር ተብለህ የተሾምክ ነህ፡፡
- እና?
- እናማ ያቅለሸልሸኛል ማለት አትችልም፡፡ ማረምና ማስተካከል ነው ያለብህ፡፡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይበት፣ መንግሥት እንዲያሻሽለው አድርግ፡፡
- አንችም እንደዛ ትያለሽ?
- ደግነቱ እግዜር አንተን አይሰማም እንጂ፣ ቢሰማህ እንደዛ ይል ነበር፡፡
- በይ ተይው ኳሳችንን እንይ፡፡
- አለቀኮ 7 ለ 0፡፡
- ሌላ ጨዋታ አለ አይደለም ወይ?
- እኔ በጧት ነው የምነሳው ልተኛ - አንተ እይ፡፡
- በጧት ምን አለ?
- በእናትህ ይህ ወንድሜ ዳያስፖራ ሆኜ ከምኖር አገሬ ገብቼ ልስራ ብሎ መጥቶ፣ እስቲ ከሁሉም በፊት መኖሪያ ቤት ልስራ ብሎ ጀምሮ አንዴ ሲከሱት፣ አንዴ የሲሚንቶ ዋጋ ሲጨምር፣ አንዴ የሱን ካርታ ለሌላ ሲሰጡበት፣ እንዲያው ምን ልበልህ፣ ሰው ለመገንባት ይህን ያህል ይሰቃያል ወይ? ብሎ በእጅጉ እያለቀሰ ነው፡፡
- አየሽ...
- አየሽ ምን?
- እንደዚህ ዓይነት የሚያናድድና በሽታ የሚያስይዝ ቢሮክራሲ ስሰማ ነው ቤት መስራት ያስጠላኝ፡፡
- እንዴ፣ እንዴ አንተማ እንደዚህ ልትል አትችልም፡፡
- ወንድምሽ ሲለው ያልተቃወምሽ ባልሽ ሲለው ምነው ገረመሽ?
- ወንድሜ የመንግሥት ቪላ፣ የመንግሥት መኪና፣ የመንግሥት ነዳጅ፣ የመንግሥት አበል፣ የመንግሥት ሞባይል፣ የመንግሥት ሥልጣን አልተሰጠውማ!
- ሥልጣን አለኝ ብዬ በደል ሳይ ላላማርር ነው?
- ላይ የተቀመጥከው ችግር ልትፈታ እንጂ ልታማርር አይደለም፡፡
- ያምሻል?
- የታመምከውስ አንተ! ድንቄም ባለሥልጣን!!
እንግዲህ ቄሶቻችሁ እንደ ውጭ ሀገሩ ስልክ ውድ ሆነውብን ከፈጣሪ እንዳንርቅ፤ ቦርዶችና የክህነቱ ባለሙያዎች የእውነቱን መንገድ ይዛችሁ አገልግሎታችሁ ሁሉ ለልዑል እግዚሐብሔር እንጂ እንደ ክቡር ሚኒስተሩ ለሰማችሁት የነቀፌታ እሮሮ ለጥቂት ግለሰቦች ብላችሁ የሌላውን ጣት ላይ መቆም አላስፈላጊ እርምጃ ነው።
ውድ ምዕመናን ሆይ! ከዚህ ቀደም ባለው ገጻችን የአስጨበጥነው ቁም ነገር አለን። እናንተም የልዑል እግዚሐብሔር ድንቅ ስራ “ቅዱስ ቅዱስ……..” እያላችሁ በምስጋና፣ በጸሎትና በምህላው በርቱ፣ እንደ ቀድሟችሁ ከደብራችሁ አትቅሩ ለሰይጣን መንገድ ይከፍታልና፣ እንደ ክቡር ሚኒስተሩ በወሬ አትፈቱ የዕምነት ፈተናው ብዙ ነውና። ደብራችሁ የትም አይሄድም ታላቁ ቅዱስ ሚካኤል ይጠብቀዋልና ነገር ግን ወርቅ በሳት እንደሚፈተን ሁሉ ዛሬ በሱ ፈቃድ የናንተ ቀላሉና አላፊው ሳንካ ስለሆነ አሁን ከጫፉ ደርሳችኃልና በጥበብና በዕምነት ጽኑ፣ እርሱ ቤቱን እያጸዳው ነውና ክብር ምስጋና ሁሉ ለእርሱ ይሁን። አሜን!!
እርሶስ ምን ይላሉ?
No comments:
Post a Comment