Wednesday, October 6, 2010

በጥሩ ሥነ-ምግባር ስለመታነጽ፡-

የርሶ ብዕር አስተያየት ተሳትፎ ሕብረተሰባችንን ይጠቅማል ያሉትን አይንፈጉን ገንቢነቱ ቦታ ይኖረዋልና!

ማሳሰቢያ፡ ይህ ገጽ የተዘጋጀው የተለያዩ የኅብረተሰባችንን ሀሳብ ለመለዋወጫ እንጂ ለሚሰጡት ማንኛውም አስታየቶች በማንኛውም መንገድ ተጠያቂ አይደለም። ጉግል ድርጅትም ኃላፊነት አይወስድም። ኃላፊነቱ በሙሉ የአስታየት ሰጪው ብቻ ነው።


በጥሩ ሥነ-ምግባር ስለመታነጽ፡-

ስለልጆቻችሁ በጥሩ ስነ-ምግባር ታንጸውና የወላጆቻቸውን እምነት ተቀብለው ጥሩ ዜጋ ለመሆን እንዲያስችላቸው የናንተ ወላጆች ቀና አመለካከት እጅጉን ወሳኝ ነው። በዚች ጦማር አማካኝነት ግንኙነታችን እየዳበረ የመጣው ውድ የዚች ገጽ አንባቢዎች እንደም አላችሁ? ልዑል እግዚሀብሔር ሁላችንንም ይጠብቀን፣ ለገናና ስሙም ምስጋና ይሁን።

እኛም ሆን በታዳሚዎቻችን የሚቀርቡትን መጣጥፍ ውስጥ በሀሳብ የምትስማሙበትና የማትስማሙባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ስለልጆቻችን ግን ከፍተኛ የሆነ አቀራረብ የማድረግ ከእያንዳንዱ ወላጅ የሚጠበቅ ነው። በተለይም የከፍተኛ ትምህርት እድል ያላገኙት ወላጆች ልጆቻቸው ከነሱ የተሻለ እድልን እንዲጎናጸፉ የሚጥሩትን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ የሚደነቅ ነው። ለዚህም የከፈሉትና እየከፈሉ ያሉትን መስዋዕት ለሌሎች በአርያነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው። በአንጻሩም ከአንድ በላይ ወይንም ለረዥም ሰአታት ሥራ የሚሰሩትና፤ በተቻላቸው ሁሉ ጊዜ ወስደው የልጆቻቸውን ትምህርትም ሆነ ከትምህርት ጊዜ ውጭ ባላቸው ማንኛውም ተሳትፎ ሁሉ ካጠገባቸው ሳይለዩ ያሳደጉና የሚያሳድጉ ሁሉ የመጨረሻውን የልጆቻቸውን የተሳካ ፍሬን ሲያዩ ምንኛ የተደሰቱና የታደሉ ይሆኑ ። ይህ በዚህ እያለ ከታዘብነው ውስጥ ብዙ ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት ስኬታማነት እንደሚጥሩ ሁሉ በልጆቻቸው ትምህርት ቤት ውስጥ የወላጅ (ፒቲኤ) ማለት የወላጅና የመምህራን ኮሚቴ ውስጥ የመሳተፍ ከፍተኛ ክፍተት ይገኛል። በተለይም በዚሁ ሀገር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም የወጡት ወላጆች ተሳትፎ የጎደለ ሆኖ ነው የሚገኘው። ይኸው ቸልተኝነትም በየቤተ ክርስትያኖቻችንም ውስጥ ጎልቶ የሚታይና ቤተ ክርስትያኖችም አስፈላጊውን መሻሻል እንዳያደርጉ አሉታን ጥሎባቸው ይገኛል።

ቤተ ክርስትያኖቻችን ከእናት ሀገር ውጭ በባዕድ ምድር በየአቅጣጫው በመከፈት ቁጥራቸው እየበዛ እንደመምጣቱ ሁሉ አብዛኞቹ ያተኮሩት ክርስትና ተነስቶና እምነቱን የተቀበለውን የአዋቂውን ዕድሜ ክልል ውስጥ ያለውን ምዕመን ጎረቤትና አንድ አይነት እምነት ካለው ቤተ ክርስትያን ለመቀራመትና በዚያው ልክ ገቢያቸውን ከፍ ለማድረግ ብቻ የታለመ ሆኖ ይታያል። ቤተ ክርስትያን አስተዳዳሪዎችም የነሱ ዕድሜ የተወሰነና የቤተክርስትያኑም ዕድሜ ውስን እንደሚሆን የተረዱት አይመስልም ወይንም እኔ ከሞትኩ እንደሚባለው አዝማሚያ እየተጓዙ ያሉ አስመስሏቸው ይገኛል፤ የቤተ ክርስቷኗን ቀጣይ መሆኑን እንዴት እንደሚያዩት ግልጽ አይደለም ወይንም ያወጡት የረዥም ጊዜ ዕቅድ የለም። የሚቀጥሯቸው ካህናትም ሆነ ወይንም በግላቸው ቤተ ክርስትያን የከፈቱት ካህናት ከምንኖርበት ሀገር አኗኗርም ሆነ ባህል ጋር የማይጣጣሙ መሆናቸው ፣ የቋንቋ እውቀት ማነስ ፣ የክርስትናውን እምነት የሌላቸውና እንደዚሁም ከኛ ትውልድ ሀገር ውጭ ለሆኑት ጨምሮ የማዳረስ ከፍተኛ ክፍተት የሞላባቸው ሆነው ነው የሚገኙት። በውጪው አለም ጨምሮ ከፍተኛ የመንፈሳዊ ትምህርቱን ያገኙት ታላላቅ የሀይማኖት አባቶችና ሊቃውንቶች ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያናችን በጎ ፈቃድና የሚመቻች መርሀ ግብር በምዕራቡ አህጉር ለምንገኝ ምዕመናንና ልጆቻችን ማቀናጀት ቅድሚያ የሚሰጡት አበይት ተግባር ነውና ጥሪያችንን በዚሁ አጋጣሚ ልናቀርብላቸው እንገደዳለን። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቋንቋውም ጭምር በቂ የሆኑ ካህናትን ማቅረቡም የዚሁ አካል ተጨማሪ ነው።

እናንተ በምትኖርበት በዳላስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ደብር በቅርቡ ከቀጠራቸው መነኩሴ አባት በዕውቀታቸውም ሆነ ባላቸው የክሕነት ማዕረግ በከተማችሁ አቻ የሌላቸውና በሚሰጡትም አገልግሎት በዕድሜ ከፍ ያለው ምዕመን እጅጉን እየረካና እየተባረከ እንደሚገኝ ከሚደርሱን መረጃዎች በጥልቁ ለመገንዘብ በቅተናል። ከሰንበት ቅዳሴ ፀሎት በኃላ ከሚሰጡት መንፈሳዊ ትምህርት ውጭ፤ ዘወትር አርብ ምሽት ከአንድ ሰአት (7 ፒኤም) ጀምሮ በሰዐቱ ተጀምሮ በፕሮግራሙ መሰረት በሰዐቱ የሚጠናቀቅ የመጽሀፍ ቅዱስ ጥናት ወይም ጉባኤን ይሰጣሉ። የዚሁ የምሽት ጉባኤ ተሳታፊዎችም ዕምነታቸውን ተንተርሶ ብዙ ግንዛቤውችን እየጨበጡና በትምህርቱም እይተባረኩ የሚገኙ መሆናቸውን ተረድተናል።

በሌላ በኩል ለልጆች ተብሎ አዲስ የተቀጠረውም ወጣት መምህር ከልጆቹ ባሻገር ለሁሉም ዕድሜ የሚስማማ የተለያየ ፕሮግራሞችን ይቀርጻል የሚል ከፍተኛ እምነት ብቻ ሳይሆን ተስፋም አሳድሮብናል። በተለይም የሰንበት ትምህርት ቤትን በተመለከተ የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘው ይኽው ወጣት መምህር ለደብራችሁ በዚሁ ዙርያ መሰረት ይጥላል ብለን እናምናለን። ለወገኖቹ አስቦ ይሁን ባናውቅም ከሶስት እጅ የሚበልጥ ክፍያን በዩኒቨርስቲ መምህርነት  የቀረበለትን ዕድል ትቶ ወደናንተ መምጣቱ ወይ የቅዱስ ሚካኤል ተአምራዊ ስራ እንጂ ሌላ የምንለው ባይኖርም፤ እርሱም በቅርቡ የዶክሪት ማዕረግ የሚያስጨብጥ ዲግሪውን ለማከል የሚያስችለውን ትምህርቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ተረድተናል። ነገር ግን ይህን ወጣት የተቀጠረበትን ፍሬ ለማየት የእርሱ ብቻ ጥረት በአጭሩ ውጤት ያስጨብጣል ከማለት በፊት፤ የወላጆች ከፍተኛ ተሳትፎን ይጠይቃል። ልጆቻችሁ ከቀለም ትምህርት ቤት ውጪ በሀይማኖታቸውም ታንጸው መውጣት (ኤ ፕላስ) እጅጉን ተመራጭ ነው። በቤተክርስትያናቸው ውስጥ የወጣቶችና የታዳጊዎች ተሳትፎ ከመጥፎ ልማድና መንገድ ብቻ ሳይሆን የሚወግዳቸው፤ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ በኮሚኒታቸው ውስጥ በጥሩ ስነ-ምግባር ታንጸው እንዲወጡ እንደሚያመቻች በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ነው። የሚያደርጉትም ተሳትፎ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥም እንደ ነጥብ የሚወሰድ ሲሆን ለከፍተኛ ትምህርትም የመመረጥ ብቻ ሳይሆን እስከ ነጻ ትምህርትም ዕድል ለማግኘትም በር ይከፍታል።

እንግዲህ የወላጆችም ተሳትፎ ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም የወጡ ወላጆች አስተዋጾ በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ ነው። የደብራችሁ አባል ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ምዕመን የሆነ ሁሉ በትምህርቱም ሆነ በችሎታው ከዚህ ወጣት መንፈሳዊ መምህር ጋር የተሳሰረ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ እያቀረብን ፣ መምህሩ ብቻውን የሚፈይደው የተወሰነ እንዳይሆን ከውዲሁ ማሳሰብ የግድ ነውና። ለዚህም ነው ልጆቻችሁንና የናንተም ተሳትፎ የተፈለገውን ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጭበጥ እንዲቻል ፣ እንደዚሁም የቤተክርስትያናችሁን ቀጣይነትና የነሱ ተረካቢነት መሰረት መጣል የሚጀመረው ዛሬ ነውና። በዚህ ዝመን ፣ ቀንና ሰአት ላይ ያልተገበርነውን፣ እንዴትስ ብለን ነው ስለ ሀይማኖታችን ቀጣይነት ተረካቢ ሳናዘጋግጅ መርሀ ግብሩን ሳንነድፍ የምናልፈው? ለዚህም የሁላችንም ተሳትፎ ዛሬውን ተጀምሮ፣ ቅዱስ ሚካኤል የሰጣችሁን መምህር በወቅቱ መጠቀም የሚገባ።

እርሶስ ምን ይላሉ?   +

2 comments:

Anonymous said...

እነ አቶ ሰላም ይህ ያቀረባችሁት ማሳሰቢያና ምክር አዘል መልክት በጣም የሚያስመሰግናችሁ ነው። በሩቅ ሆናችሁ ይሄንን ሁሉ እርዳታ ስታበረክቱልን በቅርብ ብትሆኑልንማ ምን ያህል ትልቅ ለውጥ ባመጣችሁልን ነበር።

Anonymous said...

“የፍርድ ቤት ውሎ ልዩ እትም”
በሚል ርዕስ የጻፈው ዥብ እግር እና ግብረአበሮቹ፤ ባለው የሊቀ ሊቃውንትነት ከልክ ያለፈ እውቀት በዝርዝር በመተንተን ስላቀረበ እባካችሁ አንብቡለት። ለዛውም ትንሽ እውቀት አደገኛ ነው እንዲሉ “አልቆበት እንጂ ግድቡን ቢነድለው ከነጉአዙ ጎርፍ ጠራርጎ ይዞት በነጎደ ነበር።
አይ ጉድ! አዬ ጉድ! ጉድ! ጉድ! ሞተና አረፈው! ምን ሆኖ? እንደው ምን አግኝቶት ይሆን?